top of page
AbuneGorgoryos.jpg

ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤

የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።

(መዝ. ፻፲፭ )

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

፲፱፻፴ ዓ.ም. እስከ ፪ሺ ፲፪ ዓ.ም.

(1938--2020)

ሠናየ ገድለ ተጋደልኩ፤ ብድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ዐቀብኩ፤

ጽኑ ገድልን ተጋደልኩ፤ ሩጫዬንም ጨረስኩ፤ ሃይማኖቴንም ጠበቅሁ ።

(፪ኛ ጢሞ. ፱፡፮)

የአገልግሎት ዘመን

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከአባታቸው ከቀኛዝማች ከበደ መሸሻ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ እታገኘሁ ዘለለው ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም በድሮው አጠራር በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ስማዳ ወረዳ ተወለዱ። ብፁዕነታቸው በፊት ይጠሩበት የነበረው ስማቸው አባ ኃይለ ኢየሱስ ከበደ ነበር።

ብፁዕነታቸው የልጅነት ዕድሜያቸውን ያሳለፉት ለእናትና አባታቸው በመታዘዝ፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ፊደል ቆጥረው ከንባብ ጀምረው ዳዊት፣ ጸዋትወ ዜማ እየተማሩ አደጉ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ካህን ኾኖ መኖርን ይመኙ ስለነበር ግብረ ዲቁናን አጠናቀው ክህነተ ዲቁናን በጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

-----

ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዘንድ በ፲፱፻፵፬ ዓ.ም. ተቀበሉ። ከዚያም በዲቁና እያገለገሉ ቅዳሴ ዜማ እና ቅኔ ተማሩ።

በመቀጠልም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በተመሠረተው በደብረ ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. በመግባት ቅኔ ከነአግባቡ ተምረዋል። በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም መጽሐፈ መነኰሳት በሚያዘው መሠረት በተግባር ቤት ለ፪ ዓመት በአመክሮ ረድ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ማዕረገ ምንኵስናን እና ማዕረገ ቅስናን በመጀመሪያው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እጅ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ነሐሴ ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በጻድቁ አባት በአቡነ ተክለሃይማኖት ክብረ በዓል ዕለት ተቀበሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ገዳም ዜማ ከነባህሉ፣ መጻሕፍተ ሐዲሳት እና መጽሐፈ መነኰሳትን ትርጓሜ ተምረዋል።

ብፁዕነታቸው የእውቀት ጥማት ስለነበረባቸው የቅዳሴ ዜማ ሙያቸውን የበለጠ በማሻሻል ለማስመስከር ፍላጎት በማሳየታቸው ከገዳሙ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ታላቁ ደብረ ዐባይ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ሄደው የቅዳሴ ዜማ ትምህርት በሚገባ አጠናቀቁ፡፡ ከአስተማሪያቸው ከመምህር የኋላእሸት መንገሻ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. የመምህርነት የምስክር ሰርተፊኬት ልብን ከሚመስጥ የአባትነት ምርቃትና ምኞት ጋር ተሰጣቸው። ለጥቂት ወራቶች በዚያው በደብረ ዐባይ ገዳም አስተማሪ ኾነውም አገልግለዋል። በመቀጠልም በደብረ ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳማቸው በመመለስ በገዳሙ ስመ ጥር አስተማሪ በሆኑት መምህር ልዑል ዘንድ የቅዳሴ መምህር ምክትል ኾነው ያስተምሩ ነበር።

Meskel Obituary_edited.jpg
bottom of page